የዓለም ማጣፈጫው ማር…

የዓለም ማጣፈጫው ማር…

Eros, Greek god of love


ከስምንት ወር በፊት አንድ መጽሓፍ ሳገላብጥ እግረ-መንገዴን ያነበብኩት አንድ ምዕራፍ ከዚያን ቀን ጀምሮ እንደ አንዳች ነገር እንደ ጥላ እየተከታተለ እኔን ሲያጅበኝና ሲያሳድደኝ እረፍት ነስቶኝም እንደ አውሬ ሲያድነኝ ከርሞ ነበር።…“ ይህን የመሰለ ዓረፍተ ነገር የያዘ አሜሪካን አገር እየታተመ የሚወጣውን ዕለታዊ ጋዜጣ ያነበብኩት ከጀርመን ተነስቼ በሮም አቋርጬ ሌሊቱን ቀይ ወይኔን እየጠጣሁ ወደ አዲስ አበባ በምበርበት ሰዓት ነው።
በዳዊት ብሩክ የተጻፈውን በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ„የፍቅር- ጨዋታ“ የሚለውን አርዕስት ይዞ የወጣውን ገጽ ገና ስጀምረው እኔን እራሴን ለወራት ሳይሆን ለአመታት እንደ ጓደኛ ሁኖ የሚከታተለኝን እና የሚያሳድደኝን አንድ የቆየ ጉዳይ አጻጻፉና አተራረኩ ጠቅላላ አቀራረቡ አስታወሰኝ።
ብሩክ ያነበበው መጽሓፍና ከነከነኝ የሚለው ምዕራፍና አረፍተ-ነገር በሚካኤል ኢግናቴፍ የተጻፈውን የኢሳያ በርሊንን የሕይወት ታሪክ ባዮግራፊውን ነው። ኢሳያ በርሊን የዛሬውን ቅዱስ ጴጥሮስ ከተማ የቀድሞውን ሌኒን ግራድን በ1945 ዓ .ም. ሲጎበኝ አንድ ቀን ምሽት ሳያስበው ያጋጠመውን ሁኔታ ምዕራፉ ማለት ታሪኩ መለስ ብሎ ያስታውሳል።
በርሊን በዚያን የጉብኝት ሳምንቱ በአንዱ ቀን ምሽት ምንም የሚያደርገው ነገርና ልዩ ቀጠሮ አልነበረውም።
አንድ ጓደኛው እሱ ጋ መጥቶ „ምን ይመስልኻል?…ጊዜና ምንም የምትሰራው ሥራ ከሌለህ እስቲ ወይዘሮ አና አህማቶቫን እንጎብኛት።…ከአየሁዋት እሱዋን ብዙ ጊዜዬ ነው…“ ይለዋል። በርሊን አህማቶቫ የምትባለውን ሴትዮ ማን መሆኑዋን ሳያውቅ እሽ ብሎ ተነስቶ አብሮ እሱዋ ቤት ለመሄድ ፈቃደኛነቱን ይገልጽለታል።
በሁለቱ መካከል ቢያንስ የሃያ አመት ልዩነት አለ።
ከዚያም በላይ አና አህማቶቫ ከሩሲያ አብዮት በፊት የታወቀች ትልቅ ደራሲና የቅኔ ሰው ናት። ከ1925 ዓ. ም. በሁዋላ ጠርጣሪዎቹ የሶቪየት ባለሥልጣኖች ምን ነገር እሱዋ ጽፋና አሳትማ እንዳታወጣም ከልክለዋታል።
የመጀመሪያ ባሉዋ መሠረተ-በሌለው የሓሰት ወንጀል ተከሶ የሞት ፍርድ በ1921 ተበይኖበት በጥይት ተገድሎአል። ቆይቶ በ1938 ልጅዋ እንደዚሁ በጸረ-አብዮተኛነት ተይዞ ታስሮአል። ለአሥራ ሰባት ወራት በተከታታይ ልጅዋ ታስሮባት እሱ የት እንደደረሰ ለመጠየቅ በምን ሁኔታ እንደሚገኝ ለማወቅ የእሥር ቤቱ በራፍ ላይ ከሌሎች እናቶች ጋር አብራ ቆማ አሳልፋለች።
በርሊን እንግዲህ በእንግድነት ጓደኛውን አጅቦ የሄደው እዚህች በበሰለ ዕድሜዋ ላይ የምትገኝ ቁንጅናዋ ግን ገና ያልከዳት በፈገግታ የተሞላ ፊቱዋን ሲያዩት ደስ የምትል መልከ-መልካም እና ከዚያም በላይ ጠንካራ መንፈስ ያላት አምባገነኖች ደግሞ እሱዋን የሚፈሩዋት ግን በአንድ በኩል በዓለም ጦርነቱ በሌላ በኩል በደርስባት በደል ልቡዋ የተሰበረ ጸሓፊ ቤት ነው።
ጨዋታቸውን የከፈቱት በባጥ በቆጡ አርዕስቶች ግን መልክ በአላቸው አርዕስቶች ላይ ነው። …ስለ የብርትሽ አገር ዩኑቨርሲቲና ስለ ትምህርት አሰጣጥ ስለ ጦርነት ዘመንና ስለወጣቶች ሞት ያ ጦርነትም በሰው ልጆችና እናቶችና አባቶች ላይ ስለአመጣው ስለሚያመጣው መከራና ችግር ስለ እሱ በማዉራት ሐሳባቸውን በመለዋወጥ ጊዜአቸውን አሳለፈዋል።
አንዳንድ እንግዶች በዚያን ምሽት አርፍደው ይመጣሉ። አንዳንዶቹ የመሸባቸው ተሰናብተው ይሄዳሉ።
ወደ እኩለ ሌሊቱ ላይ ሁለቱ ብቻ የእንግዳ መቀበያው ክፍል ቀርተዋል። እሰዋ በጠረጴዛው አንደኛው ጠርዝ ላይ ተቀምጣለች። እሱ ራቅ ብሎ በሌላው ጫፍ ወንበሩ ላይ ደገፍ ብሎ ከደራሲዋ አፍ የሚወጡትን ቃላቶች በጥሞና እና በትካዜ ያዳምጣል።
ስለ የልጅነት ዘመኑዋ ተወራለታለች። ስለ ኮረዳ ዘመነዋ…ታነሳለች። እንዴት ቀለበት እንደአሰረች ትዳር እንደያዘች ስለ የመጀመሪያ ፍቅሩዋ …ስለባለዋ ታስሮ መገደል ስለዚሁ ሁሉ በግሩም ቃላቶች አጫውታው ወደ ሥነ-ጽሑፍ ዓለሙ ሰለዚያ ስለመተወዳቸው-ደራሲዎችና ጸሓፊዎች፣. ፈላፋዎችና… መጽሓፍቶች ትሸጋገራለች።
በቃሉዋ በደራሲው በባይረን የተጸፈውን „የዶን ሑዋን“ ድርሰት በሚጥሙ ቅላጼዎቹዋ ስታንቆረቁረው በርሊን አላስችል ብሎት ዓይኑ ይረጥብበታል። ጆሮውን ሰጥቶአት እንዳይታወቅበት ደግሞ ፊቱን ቀስ ብሎ ወደ መስኮቱ አዙሮ በስንት መከራ የገነፈለበትን ውስጣዊ ስሜት ሁሉንም ነገር ቀስ ብሎ ይውጠዋል።ሊናገር ፈልጎአል።ግን ትቀድመዋላች።
ከእራሱዋ የቅኔ ድርሰት በቃሉዋ ጠቅሳ እንደዚሁ ከውበቱ በለሰለሰ ድምጽዋ ታካፍለዋለች። ስንት ግሩም ጻሓፊዎች በጸረ-አብዮት ስም እሥር-ቤት እንደተወረወሩ በጥይት በሶቪየቶች እነደተደበደቡና በሲባጎ እንደተንጠለጠሉ ስማቸውንና ሥራቸውን እየጠቀሰች ታጫውተዋለች።
ከንጋቱ አሥር ሰዓት ላይ ወፎቹ መንጫጫት ሲጀምሩ እነሱ አውርተው ትላልቆቹ ደራሲና ጸሓፊዎች ላይ ደርሰዋል። አለጥርጥር ፑሺኪን እና ቼኮቭን ሁለቱም በጋራ አድንቀዋል። በርሊን ቀለል በአለ አቀራረቡ ብዕሩን እንደ ሙዚቃ ቅኝት ደበላልቆ የሚያንሸራትተውን ቱርጊኔቭን አደንቀዋለሁ ሲል አህማቶቫ ስውር የሰው ልጆችን ምሥጢር እየፈለቀቀ የሚያወጣውን ዶስትዬቪስኪን ከሁሉም ደራሲ እሱንአስቀድማለሁ ትለዋለች። የቶሊስቶይና የሼክሽፒር የዳንቴና የሆሜር የሲስሮና …ስሞች አንስተው ብዙ ቦታ ደርሰዋል።
ብዙ በተነጋገሩ ቁጥር ወደ ውስጥ እየጠለቁ ሄደው ለረጅም አመታት እንደሚተዋወቁ ሰዎች ልባቸውን ከፍተው መጫወት ጀመሩ። እሱዋ ስለብቸኝነት ኑሮ ታነሳለች። ለኪነትና ለሥነ-ጽሑፍ ያላትን ፍቅርና ከዚያ የምታገኘውን ደስታ አንስታ ታሰረዳዋለች። ሚካኤል አንጂሎ ራፋኤል ሊዎራንዶ ዳቬንዥ …በርሊን ይህን እየሰማ ተመስጦ መታጠቢያ ቤት ለመሄድ እንዃን ያለበትን ደቂቃ በአንድ በኩል ጨዋታውን ላለማቋረጥ በሌላ በኩል የንግግሩዋ „እሥረኛ“ በመሆን አፉን ከፍቶ ማዳመጡን ይመርጣል።
ሁለቱም አንድ ዓይነት መጽሓፍቶችን አንብበዋል።

ሁለቱም በሰበሰቡት ዕውቀት አንድ ደረጃ ላይ አብረው ቆመዋል። ሁለቱም ስለምን እንደሚነጋገሩ በደንብ ያውቃሉ። ዓለምንም የሚያዩበት ነጻ-ዓይናቸው አንድ ነው።
በዚያን ምሽት ኢግንቴፍ እንደ ጻፈው „የበርሊን ሕይወት/…ነፍሱ ሥነ ጥበብና ሥነ -ጽሑፍ አንድ ላይ ሁነው የተገጣጠሙበት ሌሊት ነበር።“ ይለናል።
በዚህ ስሜት በርሊን የአህማቶቫን ቤት ለቆ ከእሱዋ ተሰናብቶ ወደ ሆቴሉ ይመለሳል።
ከጥዋቱ አምስት ሰዓት ላይ አልጋው ላይ ወዲያና ወዲህ እየተንከባለለ „…ፍቅር ይዞኛል።…ፍቅር ያዘኝ…“ ብሎ ጮኸ።

ምን ዓይነት ፍቅር?
„…ዛሬ የምንኖርበት ዘመን ከጥቅም ጋር ብቻ የተያያዘና ምን አገኝበታለሁ? ከሚለው ጥያቄና አስተሳሰብ ጋር የተዛመደ ነው። ዙሪያ ጥምጥሙ ሁሉ ይህ ነው በማይባል የዜና እና የኢንፎርሜሽን ዳታ የተተበተበ ነው። ችግሮችን እንኳን ለመፍታት የምንሰጣቸው ማብራሪያዎች -ሊዎን ቪስልቲር እንደ አለው- ከዚሁ ከጥቅም ጋር የተያያዘ ነው።“
ወይዘሮ አህማቶቫና ኢሳያ በርሊን አብረው ሁለቱ በግሩም ጨዋታ ሐሳብ በመለዋወጥ ያሳለፉት ምሽት ከላይኛው ከጥቅም አንጻር ከሚደረገው „ንግግርና መዘባረቅ ጋር“ ፈጽሞ የማይገናኝ ነው። ይህኛው የእነሱ ዓለምና አመለካከት ፍጹም የተለየ ነው።
የእነዚህኞቹ የአዋቂዎች ጨዋታ ከዚያና ከዚህ ከሚቦጨቀው ተባራሪ ዜናዎችና የትም ከተቀመጠ „ዳታ“ ከሚባለው ኮሮጆ ተቀድቶ ታፍሶ በአራቱም ማዕዘን የሚረጭ ሰበካ አይደለም። የልጆችም ዕብደት- ዛሬ ይህንን ነገ ያንን ሥርኣትና ኑሮ ከአልመጣም የሚልም አይደለም።


ታላላቅ የሰው ልጆች ለዘመናት ከሰበሰቡትና ከአጠራቀሙት ኮትኩተውም ጠብቀውም ለትውልዱ ከአሳለፉት ባህልና ተመክሮ ሞራልና እሴቶች …የተስተካከለ ኑሮ ለመኖር አውጥተው አውረደው ከአሰቀመጡልን ጎተረ የተገኘ ነው።


በርሊንና አህማቶቫ እነዚህ በድንገትና በአጋጣሚ የተገናኙት ሁለት ጭንቅላቶች ከዚህ „…እንዴት የተስተካከለ መልክ ያለው ኑሮ እንኑር?“ ብለው ከሚያስቡ ሰዎች ዓለም የመጡና ያንንም ባህል የጨበጡ አእምሮአቸውም በዚያ የተገነባ ኢንቴሌክቹዋል ካፓሲትአቸውም በዚያም የታነጸ ሰዎች ናቸው።
አንድ ሰው ከትላልቅ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች ከትላልቅ ጽሑፎችና ድርሰቶች የፋላስፋ ትምህርቶች ጋር እራሱን ከአላስተዋወቀና ከእነሱም ጋር በጥያቄና መልስ እራሱን ከአልፈተነ የዚህቺን ዓለም ኑሮ እንዴት እንደሆነች ፈጽሞ ሊረዳ አይችልም።
እዚያ ውስጥ ገብቶ ከዋኘ ደግሞ ምን ያህል ብሩህ የሆነ ዕውቀትና ጥበብ አግኝቶ እሱ በሚሰጠው ፍርድና ሥራው ለሌላውም ሰው በሚያካፍለው ትምህርቱ ሕያው ሁኖ ይኖራል።
ሕይወትም የሰው ልጆች ሕይወትም የተንኮለኞች መቀለጃ ሳትሆን ወርቅማ መሆኑዋን ይረዳል። የሞራል እና የሒሊና ፍርድም ማንኛቸውም እርምጃችን የፖለቲካ ይሁን የኢኮኖሚ የማህበራዊ ኑሮ ይሁን… የትዳር እራሱ የመልካም ጉርብትና አብሮ የመኖር ብልሃት ከዚሁ እላይ ከተባለው ዕውቀት ይመነጫል።
አህማቶባና በርሊን ሊግባቡ ዓለምን በአንድ ዓይን ሊያዩ የቻሉት ከመጽሓፍት-ከተለያዩ መጻሕፍት ለቅመው ሰብስበው ከአገኙት ዕውቀት ነው።
ለዚህ ነው መንፈሳቸው አንድ የሆነው። አመለካከታቸው አንድና ኩታ ገጠም የሚመስለው። ቋንቋቸውም አንድ ሆኖ በቀላሉ ሊግባቡ ችለዋል። ይህም እነሱን አንድ አድርጎአቸዋል።
የጋራ ቋንቋቸው ይህቺን ዓለምና -ለብዙዎቹ ስውር የሆነውን የእኛን የሰው ልጆች ባህሪን – ጥሩ አድረገው ያቀረቡት የጸሓፊዎች የተጠቀሙበት„የሥነ-ጽሑፍ ቋንቋ ነው።“
ያ ምሽት ሕያው ሁኖ የሚቆይ የሁለት ሰዎች „ትስስር“ ነበር። እንደዚህ ዓይነቱ ትስስርና ፍቅር ደግሞ በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ አንዴ ወይም ሁለቴ የሚመጣ ነው።
በርሊንና አህማቶቫ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገው ጥለው በአንዴ ተግባቡ። በብዙ መንገዶች ሁለቱም አንድ ሆኑ። በመካከላቸው በቅጽበት የበቀለው አንድነት ሁሉንም ነገር ረስተው ልብ ከልብ እንዲገናኙ አድርጎአቸዋል።
ስለዚያ ምሽት ያቺ መልከ መልካሙዋ አህማቶቫ የጻፈቺውን ግጥም ዛሬ የሚያነብ ሰው ሁለቱ ተዋደው አንድ አልጋ ተቃቅፈው ጊዜውን ያሳለፉ ሊመስለው ይችላል። ግን ኢግናቴፍ እንደጻፈው ሲሰነባበቱ እንኳን ተቃቅፈው ከመሳሳም አላለፉም ነበር ይላል።
የፍቅር ቁርባናቸው ኢንተሌክቹዋሊ- በአእምሮ ጥበብና በዕወቀት ላይ ብቻ ነበር። ይህም ጥሩ መንፈስና መልካም አመለካከትን በሁለቱ መካከል ፈጥሮአል።
“ፍቅር” ወንድማዊና እህትማዊ ፍቅር ማለት ይህ ነው። ጓደኛሞች እጅ ለእጅ ተያይዘው ይህቺን መከራ የምታሳየንን ዓለም ለመቀየር አብረው የሚቆሙት በዚህ መንፈስ ነው። በርሊንና አህማቶቫም ያደረጉት ይህንኑ ነው።
ለበርሊን ያ ከአህማቶቫ ጋር ያሳለፈው ምሽት የማይረሳው ነው።

እሱዋ እዚያው ሶቪየት ኅብረት እዚያ ውሸትና ፍራቻ በነገሰበት አምባገነን ሥርዓት ውስጥ ቀርታለች። ወደ ነጻው ማህበረሰብ ተመልሶአል።

ትንሽ ቆይቶ ሥርዓቱ እሱን በርሊንን እቤቱዋ ተቀብላ በማነጋገሩዋ-ከብርቲሽ ሰላይ ጋር ተንኮል ትጠነስሳለች ተብላ ከደራሲዎች ማህበር እንድትባረር ተደርጎአል።


ልጅዋ ወህኒ ቤት ይወርዳል። በርሊንን በመገናኘቱዋና ከእሱ ጋር ወርቅማ አስተሳሰቦችን በመለዋወጡዋ እሱን አንድ ጊዜም ተጸጽታ በጽሑፎቹ ላይ ግን ይህቺ ትልቅ ደራሲ ቀኑን አልወቀሰችውም።” …የሚለውን አስሰተሳሰብ ዳዊት ብሩክስ አስፍሮ በሚከተሉት ቃላት ሐሳቡን ይዘጋል።


„…እግዚአብሔር በሰጠኝ የዕድሜ ጸጋ በእንደዚህ ዓይነት ቁርባንና ወዳጅነት ትላልቅ ጽሑፎችንና /ትላልቅ አስተሳሰቦችን አብሮ እያጠኑና እኩል እየተከፋፈሉ ለመኖር የወሰኑ ሰዎችን ስም ለማስታወስና ለመቁጠር እችላለሁ።

ግን አሁን በዚህ በያዝነው ክፍለ ዘመን እኔ እርግጠኛ አይደለሁም ስንት ሰዎች ለእንደዚህ ዓይነቱ ቅዱስ ሥራ ዝግጁ እንደሆኑ አላውቅም።… ለእንደዚህ ዓይነቱ የመጽሓፍት ፍቅር ምን ያህል ትምህርት ቤቶችም (አስተማሪዎች)ተማሪዎቻቸውን አበረታትተውና ኮትክተው ያዘጋጁ/አያዘጋጁ እኔ የማውቀው ምንም ዓይነት ነገር የለም።“
ይህን ጽሑፍ እያነበብኩ ስጓዝ እኔን እንደ ጥላ ይከተለኝ የነበረው ነገር የዚያን ምሽት እንደገና በአእምሮዬ ብቅ አለ።


እሱም አንደኛው ዳዊት ብሩክ እንደአለው በመጽሓፍትና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የሰዎች ወዳጅነት በእኛ በኢትዮጵያኖች መካከል „…የኢንተለኬችዋል ኢሞሽናል ስፕሪሽዋል…ማለት የአእምሮ የመንፈስና የልብ ጓደኝነት…“ በመካከላችን መጥፋትና ማጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ „…ለነጻ-አስተሳሰብና ለነጻ- ሕብረተሰብ…ለዜጋ ነጻነት ያለን ፍቅር በቶታሊቴሪያን አስተሳሰቦች ተጨፍልቆ መደማመጥ በመካከላችን በመጥፋቱና ጫጫታ በአገራችን በመንገሡ ምን እናድርግ?መድሃኒቱስ ምንድነው የሚለውን የቆየ ጥያቄዬን እንደገና ቀስቅሶብኛል። ከጥበብ ውጭ ሌላ መፍትሔ የለም።

1) በነገራችን ኢሳያ በርሊን ስለ ሁለት ዓይነት „ነጻነት“ በጽሑፉ ላይ ደግሞ ደጋግሞ ያነሳል። አዎንታዊና አሉታዊ ነጻነት።

2) በሠለጠኑ የአውሮፓ አገሮች አዋቂዎች የጥናት ክበብና የጥናት ማህበራት አላቸው። ይህም ሙዚቃንና እስፖርትን ሥዕልና… ያካትታል።

ለ አእምሮ ሰኔ 2006 / June 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 10

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s