ነጻነት ወይስ ባርነት ? ሥልጣን እና የሰው ልጆች!

bokassa-crowned3

ነጻነት ወይስ ባርነት?

*

ሥልጣንና ሰው!

evil

 

የገዢዎች የረቀቀ ብልሃት ጠንክሮ የዜጎችች ፍረሃት ግልጽ ሁኖ የሚታይበት ቦታ አፍሪካ ነው። እንደልባቸውም አምባገነኖች የሚርመሰመሱበት አንድ የቀረች ሜዳ አለ ቢባል እዚያው:- አፍሪካ ነው። ግን ማነው አምባገነን? ማነው የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ አራማጅ? ማነው ለዲሞክራሲና ሰበአዊ መብቶች መከበር የቆመው ? ይህን መረዳት ደግሞ እዚያ አስቸጋሪ ነው።

Castro-Mengistu_full


በብዙ ቦታ፣ በዓለም ዙሪያ፣ አምባገነኖችና የቶታሊቴሪያን ፍልስፍና አራማጆች ተባረዋል።
በአሜሪካና በካናዳ ዱሮም ቢሆን የሉም። አልነበሩም። በአውሮፓ ከሃያ አመት በፊት ድራሻቸው ጠፍቶአል። በደቡብ አሜሪካ ነጻነታቸውን ተቀምተዋል። በእሲያ ቁጥራቸው በጣም እየቀነሰ መጥቶ አንድና ሁለት አገሮች ብቻ አምባገነኖቹን ለጉድ ታቅፈው ቁጭ ብለዋል።

 

mugabe በአፍሪካ ግን ማንም እንደሚያውቀው ተራብተው ተባዝተው እግራቸውን ዘርግተው ተቀምጠዋል። አንዱን ከአንዱ መለየት ያስቸግራል። ይህም በመሆኑ ትክክለኛ አመለካከት በዚህ ጥያቄ – በነጻነትና በባርነት – ላይ የለም።

አንዱን ተገላገልን ስንል ሌላው ከተፍ ይላል። አንድን ሕዝብ መከራ አሳይቶ ጊዜ የጣለውና የተባረረውም – እሱ አያፍርም እንደገና ለመምጣት ሽር ጉድ ይላል።
ከፊሉ ዕድሉን ለመሞከር ዱር ገብቶአል። ሌላው ከተማውን ይዞአል። የተቀረው ስደት ወርዶ ጊዜውን ተራውን ይጠብቃል።
dictators-in-arms

በትናንሽ ቡድኖች በየአለበት እንደምናየው ቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ በስውር የሚያራምዱ ሰዎች ተሰባስበዋል።

በጋዜጣ አታሚዎች ቢሮና በቴሌቭዠን ጣቢያዎች እነዚህ አምባገነኖች ተሰግስገው ተቀምጠዋል። የአፍሪካ ቤተ-መንግሥት የእነሱ መግቢያና መውጫ ማደሪያቸውም ሁኖአል። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን በአፍሪካ በብዙ አገሮች እነሱ ተከፋፍለው አስፈራርተው ይዘዋል።

መንገድ ላይ ትላልቅ መኪናዎቻቸውን ይዘው „ልቀቁ“ እያሉ እግረኛውንም ሹፌሩነም ሲያባርሩ እንመለከታቸዋለን። አደባባዩና ቡና ቤቱ ሆቴሉና ባንኩ በእነሱ ቁጥጥር ሥራ ነው።
የፖሊሲ ሠራዊቱን ቤታቸው ቁጭ ብለው ያዙታል። ዳኛውን ትዕዛዝ እየሰጡ ያራውጡታል።

ወታደሩን በፈለጉበት ቦታና ሜዳ በቀንና በማታ በብርድና በቁር በሁሉም አቅጣጫ ያሰማሩታል።

መሸት ሲል ደግሞ በቴሌቪዥን ብቅ ብለው ማን እንደሆኑ ፊታቸውን አስመትተው ዞር ይላሉ። መንገድ ላይ ሽጉጥና ጠበንጃቸውን ይዘው ይንጎራደዳሉ።

ሌሎቹ እምባገነኖች -ይህ ነው አንዱ የአፍሪካ ሌላው ችግር- በየፊናአቸው ጫካ ገብተው „ሥልጣን „ ላይ ለመውጣት እርስ በእራሳቸው ሳይቀር መዋጋቱን ተያይዘውታል።armed-uprising
ገዢውን መደብ አምባገነኑን እነሱ ደፍረው በማስፈራራታቸው ብቻ ትናንሾቹን – የሚመጣባቸውን ሳያዩ- „በርቱ“ የሚሉ ተበራክተዋል። ጥቂቶቹ ትናንሽ አምባገነኖች መጪውን ዕድሉን ለመጠቀም በመሰባሰብና በመደራጀት ላይ ይገኛሉ። „…እኔ እሻላለሁ። እኔ አውቅልኻለሁ። ይህን ልበስ። ይህን ቅመስ። ያን ተው። መገንጠል ከፈለግ እኔን ተከተል። ….ጊዜው ዘንድሮ የእኛ ነው !“ ባዩ ብዙ ነው።

የገዢውን ቡድንም ሆነ የተቃዋሚውን ሠፈር አንድ በአፍሪካ አህጉር የሚያደርግ ነገር ቢኖር ሁለቱም በአምባገነን አስሰተሳሰብና ፍልስፍ በርዕዮተ-ዓለሙና በፖለቲካ ጉዞው እነሱ – በርካታ ጥናቶችና ብዙ ተመልካቾች በግልጽ እንደሚሉትና በዓይንም እንደሚታየው- „የተጠመቁ“ ናቸው።

ለምንድነው አምባገነኖች ከሌላው ዓለም ተራ በተራ የተባረሩት? እንዴትስ ነው የተባረሩት?…ለምንmubarekድነው በአፍሪካ በየጊዜው በተለያዩ ስሞች እነሱ እዚያ የሚፈለፈሉት?

ለምንድነው አንዱ አምባገነን ሲወድቅ በሌላው ከእሱ በአልተሻለው አምባገነን የሚተካው? ለምንድነው ዓለምና ሰው ሁሉ በአፍሪካ ይህንን ሁኔታ ዝም ብሎ የሚያየው?

ብዙ ቦታ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቀለምና ስም የተደራጁ አምባገነኖችና ተከታዮቻቸው ተራ በተራ እነሱ -በርካታ ጽሑፎች እንደሚመሰክሩት- መድረኩን ለቀው ተሰናብተዋል። በአፍሪካ ግን መሽገው ተቀምጠዋል።

ben-aliቁጥራቸው ሳይቀንስ በእያንዳንዱ አገር ቢያንስ ከሃያና ሰላሳ ድርጅቶች በላይ ሁነው ሜዳውን ይዘውታል።

በሱዳን ከጥቂት አመታት በፊት አንድና ሁለት ነበሩ። በናይጄሪያ እንደዚሁ ትንሽ ነበሩ። በኮንጎ በጣት ይቆጠራሉ። በኢትዮጵያ ከጥቂት አመታት አንድና ሁለት ሦስት እና አራት ነበሩ ።

አሁን ግን ከፖርት ሱዳን እስከ ደቡብ ሱዳን ከኮንጎ እሰከ ምዛምቢክ፣ በሱማሌና በሊቢያ… ከኤርትራ እሰከ ኡጋዴን ከአፋር እሰከ ደንቢዶሎ ከወልቃይት እሰከ ሞያሌ የአምባገነን አስሰተሳብ ተከታይ ድርጅቶች ቁጥር በምዕራብ አፍሪካና በመካከለኛው በምሥራቅና በደቡቡ- አፍሪካ ጨምሮ ተበራክቶአል።gahdafi

„ኤርትራውና ትግሬው“ አንዱ እነደጻፈው “ አትረብሹኝ ለብቻዬ ለብቻችን እንግዛ “ ይላሉ። እነሱን አይተው „…የኦሮሞና የኦጋዴን ድርጅት መሪዎች ደጋግመው እነደሚሉት እኛም ተገንጠለን እኛም ዕድሉ ደርሶን ብቻ እንግዛ …“ ይላሉ።

እንደሚባለው…አማራው አሁንም ይገባኛል ባይ ነው።…አፋሩ ጉራጌው የደቡቡ ሕዝብ ተወካይ ግለሰቦች ሌላ ልዩ ልዩ ነገሮች ያነሳሉ።… በዚያ ላይ መድረክ አማራጭ ኦብነግ ኢህአዴግ መኢሶን ኢህአፖ ደርግ ግንቦት ሰባት (አዲዩ አለች?)…ደቡብ ሕዝቦች ….የሚባሉ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በይገባኛል ጥያቄ ተያይዘዋል ።“

„… ሁሉም -ሌላው ከንቱ ነው- ለአገሪቱ ችግር/ ስለ አንተም ጉዳይ ፍቱን መፍትሔ የአለኝ እኔ ብቻ ነኝ „ባይ ሁኖአል። ይህን ማለት ተገቢ ነው? ይህን ማለት ስተት ነው?

ለምንድነው ተቃዋሚውም ቡድን ሆነ ገዢውም መደብ „እኔ ብቻዬን አውቃለሁ“ በሚለው በቶታሊቴሪያን ፍልስፍና እና አስስተሳሰብ የተማረኩት?

ለምንድነው ሕዝቡና የአገሪቱ ዜጎቹ በአምባገነን አስተሳሰብ አራማጆች በቀላሉ በአለፉት አርባና ሃምሣ አመታት በትንሹ ለመቁጠር የተታለሉት?… ወይም የተማረኩት? …አሁንም በዚያው አስተሳሰብ ላይ እነደ ቆረበ ሰው የረጉት?
እሱን ስንል የሃይማኖት አክራሪዎች ብቅ ብለዋል። እሱን ስንል መለዮ ለባሽ ወታደሮች ስለ አስተዳደር እናውቃለን ብለው እንደገና አንሰራርተዋል።

ለመሆኑ ዲክታተሮች እንደሚነግርላቸው እነሱ“ ጂኒየስ“ ማንም የማይደርስባቸው ብሩህ አእምሮ ያላቸው ሰዎች ናቸው? …ወይስ „ሳይኮፓት“ …„ዕብዶች ናቸው“? stalin

ወይስ „…ልዩ ፍጡር? እግዚአብሔር ለቅጣት የላካቸው? ወይስ አንዳች ዓይነት ከጨለማ ቤት የተላከብን „ዲያቢሎስ የሚጋልባቸው“? ይህ ከአልሆነ…የቶታሊቴሪያን አስተሳሰብ አራማጆች ታዲያ ምንድንናቸው?hitler

እነዚህን ጥያቄዎች አንስተን (በአንድ ቀን ፈጽሞ አብራርተን አንጨርሰውም) ቀስ እያልን እያዘገምን ችግሩን ከበን ጥያቄውን አገላብጠን ለመመለስ፣ ለመፍታት እንሞክራለን !

የፖለቲካ ቲዎሪ/ቲዎሪዎች-ብዙ ይመስላሉ እንጂ ወዳጄ- በጣም ጥቂቶችና በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ወደ ሥልጣን የሚወስዱ መንገዶችም ወደዚሁ ወደ ሥልጣን የሚያደርሱና እዚያው ሥልጣን የሚያቆዩ ብልሃትና ዘዴዎች -ቴክኒኮቹም ውስን ናቸው። እነሱም በዚህች ዓለም አንድ ሁለት ተብለው ይቆጠራሉ።


bokasንጉሥ ቦካሳ አገሪቱን በዚያውም ሕዝቡን ለመቆጣጠር የተጠቀመው ዘዴና ብልሃት ከኢዲ አሚን ዳዳ idi-aminአይለይም። የሁለቱ ብልሃት ከመንግሥቱ ኃይለማሪያም፣ የመንግሥቱ ኃይለ ማሪያም ጉዞ ከኢሳያስ አፈወርቂ፣ የእሱ አካሄድ ወይም የእነሱ ሁሉ ጉዞ… ከካስተሮና ከማኦ ከስታሊንና ከኪም ይህ ሁሉ ደግሞ ከሆቺሚንና ከፖልፖት ብልሃት እምብዛም አይርቅም።

የምናወራው -እንደማመጥ ከአልን- ስለ አገዛዝ ብልሃትና ወደ ሥልጣን ወደሚያወጣው ቴክኒክ ነው! ሒትለር ደመኛ ጠላቱን እስታሊንን በሥራውና በቆራጥነቱ -ተጽፎ እነደሚነበበው- እጅግ አድርጎ ያደንቀው ነበር። leninሞሰሊኒ ሌኒንን። ሁለቱ ደግሞ ማኪያቬሊን ያመልኩ ነበር ።

ሁሉም (ቁጥራቸው ብዙ ነው በስም ይለያያሉ እንጂ) ከታች ተነስው ነው እዚያ ማንም ተንጠራርቶ ደርሶባቸው ሊያወርዳቸው የማይቻልበት ዙፋን ላይ – አለ የሕዝብ ምርጫ ፍላጎትና ልመና ሊቀመጡ የቻሉት የተወሰነ ብልሃት በመጠቀማቸው ነው።

ምን ዓይነት ብልሃት ነው እነሱ የተጠቀሙት? mussoliniምን ዓይነት አመቺ ሁኔታ አግኝተው ነው? እነሱ እዚያ ላይ መጥቀው ወጥተው የቤተ-መንግሥቱ አልጋ ላይ በቀላሉ ለመውጣት የቻሉት?

እንዴትስ ለረጅም አመታት አረፍ ብለው ለመግዛት የቻሉት? በምንስ ብልሃት ነው ተቀናቃኞቻቸውን እንዳይደርሱባቸው ሥልጣናቸውንም እንዳይጋሩአቸው ከሩቁ እዚያው በአሉበት ማቀው እንዲቀሩ ያደረጉት? የሥልጣንና የኃይል ዘዴው ምንድነው?

ሳዳም ሁሴንና ጋዳፊ ገማል አብደልናስርና ቾምቤ አዚዚና አያቶላ ሆሜኒ ታሊባናና አልባሽር ሁፌት ቧኜና ሴክቱሬayatolla …እነዚህ ሁሉ ከታች ተነስተው -ዘውዱን እንደ ቦካሣ መድፋት ብቻ ነው አንዳዶቹ የቀራቸው- እላይ ማንም እነደሚያውቀውና እንደተመለከተው የተንጠለጠሉ ሰዎች ናቸው።

በምን ብልሃት ነው? በምን ተዓምር ነው? ተራ ሰዎች ዓላማቸው በቀላሉ ለእነሱ ሊሰምር የቻለው?


bokassacrownedከእነዚህ ሁሉ የፈረንሣዩን ናፖሊን ፖናፓርትን አረአያው አድርጎ ሥልጣን ወጥቶ በሃያኛው ክፍለ ዘመን እንደ እሱ እንደ ናፖሊዮን ዘውዱን አናቱ ላይ ደፍቶ ወደሚስቱ አክሊሉን ሊጭን ዞር ያለው ሰው እላይ እንደተባለው„…ንጉሠ ነገሥት „ ቦካሳ ብቻ ነው።

ቦካሣ ማንም ይህ ሰው ተንጠራርቶ አንድ ቀን እዚያ መሰላል ላይ ይወጣል ብሎ ያልገመተው ሰው ነው። ማንም ይህን ሰው ለንጉሠ-ነገሥትነት አላጨውም።

ግን ደግሞ ከእሱ በምንም ዓይነት ያላነሰ ፈላጭ ቆራጭ ሥልጣን የነበራቸው ሰዎችን የ20ኛው ክፍለ-ዘመን – እንደ ሌኒንና ሞሰሊን እንደሒትለርና እንደ ስታሊን እንደ ካስትሮና እነደ ሆኔከር እንደ ቻው ቼስኮ እንደ …ያሉትን ሰዎች ይህቺ ዓለም አስተናግዳለች።
kim-ilsung እነሱስ እንዴት ሥልጣን ላይ አምልጠው ወጡ? እንዴትስ ሥልጣናቸው ላይ ከረሙ?

ይህን እና ይህን የመሰሉ ጉዳዮችና ጥያቄዎች አንስተን ከዚህ በፊት በጀመርነው የኢንላይትሜንት -የብርሃን ጉዞ ጥረታችን መልስ ለመስጠት ሙከራ አናደርገናል።

እንግዲህ በጀመርነው ሓሳብ እንቀጥልበት። ሁሉም የድርጅት መሪ በአፍሪካ እንደ „ቦካሣ ነው“ ብንል ዘለፋም ወቀሳም ወይም ደግሞ ሙገሳም አይደለም ።
ትልቁም ትንሹም „የቶታሊቴሪያን አጋንንት“ በአፍሪካ ሆነ በሌላ አካባቢ እንደ „ንጉሥ ቦካሣ“ – በሕዝብ ሳይመረጥ- ቢያንስ አንድ ቀን ብትሆንም ቤተ-መንግሥት ገብቶ በሰው ላይ ቀልዶ በሕይወቱ ለትንሽ ደቂቃና ለጥቂት ቀናት – አመታቱንማ የሚመኘው ብዙ ነው- ተደስቶ መሞት ይፈልጋል።
ለምን?

ይህ ፍላጎት ይህ ምኞት ከየት መጣ ? የሰው ልጅስ ለምን ይህን ያልማል?

ሌላ ጥያቄ።

ለመሆኑ በአፍሪካ ይህን ማለም ሲቻልና ይህን ማድረግ „ሲፈቀድ“ ሌላውስ ጋ ለምን ወይም በምን ምክንያት እንደዚህ ዓይነቱ ቅዠት „ይከለከላል“?

…ለመሆኑ በምን ዘዴ አድርገው እነሱ ተቆጣጥረው ያዙት?

ተወደደም ተጠላም፣ አውቀንም አላወቅንም ምናልባት በቃላት ጨዋታ መታለልም አለ- ብዙ ሰው ብዙ „አምባገነን ቦካሣዎችን“ ዝም ብሎ ተቀብሎ በትከሻው ላይ ጭኖ እነሱን „በደስታም ወይም በሐዘንም“ በደንብ „የማስተናገድ በሽታም“ በዓለም ላይ -አከባቢአችንን ማየት ይበቃል-ይታያል። ለምን እነደዚህ ሆነ?

…ይህ ደግሞ ምክንያት አለው።

የሰው ልጆች በአንድ በኩል በባሕሪአቸው ደካማ ናቸው። በሌላው ጎኑ የሰው ልጆች መንገዱን የሚያሳያቸው መሪ/መሪዎች ይፈልጋል። አንደኛው ምክንያት„ደህና ቀን ይመጣል“ ብሎ በተስፋም ያንቀላፋል። „ሆዳም!“ – ብዙዎቹ እንደሚሉት- ብቻ ሳይሆን „…ምን አገባኝ ልጆቼን ላሳድግበት፣ ለምን የእሳት ራት ልሁን …“ብሎም ሊያስብ ይችላል። አልፎ ተርፎም „…ሁሉም አንድ ናቸው።… ልዩነት በመካከላቸው የለም።… ያም አምባገነን ይህም አምባገነን… „ ብሎም እርሙን አውጥቶ ተስፋ ቆርጦም ይሆናል። (አንድ ሰው ደግሞ አይቶ አውጥቶ አውርዶ ይህን ከአለ አይፈረድበትም!)

የሰው ልጅ/ልጆች -ጥቁሩም ነጩም- ከገባበት ችግር የሚያወጣውን „አለቃ“ ፈልጎ ከአገኘ ይከተለዋል።

አንዳንዴ ሌላው ብድግ ብሎ የተከተለውን መሪ „…ይኼ ሁሉ ሰው አይሳሳትም „ ስለዚህ “እኔም ብቻዬን ከምቆም” ብሎ እራሱን አታሎ እሱም ተነስቶ አብሮ ይጮሃል።dictatorship1

ይህን የተገነዘበ አንድ እሳት የላሰ መሪ ደግሞ ጸሐፊዎች በትክክል እንደአሰፈሩት „…እንደ ከብት አንድ ቀን የሚነዳውን አገልጋይ ተከታታይ ወይም የሚሞትለትን ከመሞት የማይመለሰውን ሎሌ“ ቀስ በቀስ „ሳይታወቅበት በብልሃት ኮትኩቶ አዘጋጅቶ አስታጥቆ ወደ ጦር ሜዳ ይልከዋል።“ እንዴት? በምን ዘዴ?

የሰው ልጆችን ከገቡበት ችግሮች ጎትቶ የሚያወጣ „መሪ ነብይ“ አንድ ሳይሆን እነሱ “ብዙ” ናቸው። እንደሚታወቀው የተለያዩ መሪዎች እኔ እሻላለሁ እኔ እብልጣለሁ ብለው ይነሳሉ። እነሱም የሰውን ልጆች አእምሮ „አስክረው ለመያዝ“ ታሪክ ላይ ብዙ አካባቢዎች እንደምናየው “የሰበካ ፉክክር” ውስጥ ገብተው ይገጥማሉ።

አንዱ ቡድን(- ኢትዮጵያን -ጥሩ ምሳሌ ናት -) ተነስቶ አንድ ነገር ይላል። ሌለው ቡድን ለየት ያለ ብልሃት ይቀይሳል። ሦስተኛው ሁለቱን ገፍትሮ የራሱን አዲስ አስተሳሰብ ለማስፋፋት ይሞክራል። አራተኛው ዱላ ወይም ጠበንጃ ይዞ ሁሉንም ጭጭ ለማድረግ ይነሳል።
አምስተኛው ላስታርቅ ብሎ ቤንዚን አርከፍክፎ እሳቱን በሁሉም አቅጣጫ ይለኩሳል። Nibelungen-Gemetzel-an-Etzels-Hofስድስተኛው ከጎረቤት ጠላት ከባዕድ ጋር ገጥሞ ሁሉንም ለመውጋት መላ ይመታል። ሰባተኛው ኅብረትና አንድነት ብሎ ከፋፍሎ ተራ በተራ ተቀናቃኞቹን መቶ ኮርቻው ላይ ጉብ የሚልበትን መንገድ ያመቻቻል። ስምነተኛው ….ረጋ ብሎ የሚያስብ ሰው ደግሞ ለመሆኑ ትክክለኛው ከእናንተ ሁሉ ማን ነው? ብሎ ይጠይቃል።

ለመሆኑ ከእነሱ ሁሉ ትክለኛው ማን ነው? ሁሉም? …ወይስ አንዱ? ወይስ የተወሰኑት? ወይስ ሌላ ገና ያልተወለደው?

….ብቻ! እዚህ ላይ አንድ ሓቅ ቢጠቀስ በሰው ልጆች ላይ በተለያዩ አካባቢዎች – ከድንጋይ ዳቦ ዘመን – ከኦሪት ዘ-ፍጥረት እስከ አሁን ጊዜ ድረስ እስከ 21ኛ ክፍለ-ዘመን በአታላይ የፖለቲካ መሪዎች ብልጣ ብልጥነት ብዙ እጅግ ብዙ ተቀልዶበታል።

መቀለድ ብቻ ሳይሆን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች- አንደኛና ሁለተኛ ዓለም ጦርነት ተመልከት፣ በመደብ ትግል ስም የተለኮሱትን ጥፋቶች መለስ ብለህ እይ፣ በማራኪ ስም የተካሄዱትን አብዮቶች ቁጠር፣…የብሔር ትግል የሚባለውን የሕዝቦች ፍጅት ጨምረህ አብረህ አስተውል- በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ንጹህ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የፖለቲካ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ የሃይማኖትbinladen „አባቶችም“ እንደሚባለው „አታላይ ነቢዮችም“ (ስለ የተለያዩ የዓለም ሃይማኖቶች ነው የምናወራው) በሰው ልጆች አእምሮና ልብ iranላይ ቀልደው ወደሚፈልጉበት መንደርና ሠፈር -ደም እየፈሰሰ- ሰውን እየነዱት አስገብተዋል።

እንግዲህ ለመሆኑ የትኛው የፖለቲካ ቲዎሪ ነው ከሁሉም ዕውነተኛው? የትኛው እምነት ነው ከአሉት እምነቶቹ ሁሉ ትክክለኛ ነው?…የዱሮው ሃይማኖት ወይስ አዲሱ? የዱሮ ፖለቲካ ወይስ አዲሱ?
አምባገነኖች ከአውሮፓና አሜሪካ ተባረዋል።… እንዴት ተባረሩ?
አንዴትስ አምባገነኖች በአፍሪካ ብቻ መሽገው ተረፉ?

የአምባገነኖች አካሄድና ጉዞ፣ የፖለቲካ አመለካከታቸው፣ ዓለምንና ሰውን የሚያዩበት ዓይናቸው እንዴት ነው?

ለመሆኑ አምባገነኖች ምን ይፈልጋሉ? ምንድነው አነሱን “የሚያስደስታቸው ነገር”?

ለምንድነው አንድ ሰው ሥልጣን ሲወጣ ልዩ ፍጡር ሁኖ ታይቶበትና ተሰምቶበት የማይታወቅ ባህሪና ገጽታ የሚያሳየው?

ለጊዜው „የብሔር/ብሔረሰብን ጥያቄ የሚባለውን ነገር…የኤርትራን ነጻነት ጉዳይ „ ወደ ጎን እናድርገው።

የኦሮሞን መገንጠል፣ የኦጋዴንን ጥያቄ የፖለቲካ ደርጅቶችን አላማና ግብ – እነሱንም ለጊዜው- ይህን ጉዳይ እናሳድረው።

የዳቦና የሥራ የጡረታና የጤና የሕክምና እና የትምህርት በብዙ ሚሊዮን የሚቄጠሩ ሰዎችን የሚያሳስበውን የዋጋ መወደድ የማደሪያ ቦታ ማጣት …አነዚህን ሁሉ ለጊዜው ለነገ እናስተላልፈው።

በእሱ ፋንታ ነገሮችን በቅጡ ለመረዳት „የሥልጣን ሰዎችን አስተሳሰብ ከእነሱ ጋር ወደ ሥልጣን እርካን ለመውጣት“ የሚፈልጉትን ሰዎች ባህሪ ምን እንደሆነ መለስ ብለን እንመልከት።

ሮበርት ግሪን፥ “ስልጣንና አርባ ስምንት መላዎቹ”
Robert Greene „Power – the 48 laws of Power“

power-guides

በሚለው አስደናቂ ጽሑፉ በአለፉት ሦስት ሺህ አመታት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥልጣን የሚወስደውን ለአንድ ተራ ሰው ለማወቅ ሆነ ለመረዳት ድብቅና አስቸጋሪ የሆነውን የብልሃተኞች መንገድ ቁጭ ብሎ አጥንቶ እሱ በአወጣልን መጽሓፉ ላይ የሚከተሉትን አብይ የሆኑ ፍሬ ነገሮች -እነሱ ማን መሆናቸውን እንድንረዳ – እንደሚከተለው አስቀምጦልናል።
„…በአንደኛ ደረጃ ዓላማህን ለመምታት ከፈለግህ አለቃህን ከመሬት ተነስተህ እሱን አትፈታተነው። አትፎካከረው ።

ወዳጆችህን የትግል ጓደኞችህም ቢሆኑ እነሱን አትመናቸው። ጠላቶችን እንዴት እንደምትጠቀምባቸው ግን ሁል ጊዜ አሰላስለህ መላ- ምታ። ከመምታትም ችላ አትበል።እቅድህንና የመጨረሻ ዓላማህን ለማንም ሳትናገር በልብህ ለራስ ብቻ ያዘው። በምንም ዓይነት የጠበቀ ግንኙነት ከማንም ሰው ጋር አታድርግ። ያገኘኸውን ሰው ግን አጥንተህ አስጠግተህ እሱን ያንተ ታማኝ ሎሌ ከማድርግ አትስነፍ።


ሌሎቹ ለአንተ እንዲሰሩልህና በአንተ ሥር እንዲሰሩ ይህን ከማድረግ አትስነፍ። እነሱን ከማድነቅና ከማሞገስ ችሮታም ከመስጠት ችላ አትበል።

ዕድለ ቢስ የሆኑ ሰዎችና ቀና ነገር የማያስቡ ሰዎችን ከአንተ አጠገብ አታድርስ ። አርቃቸው።

ሊያታልሉህና አታለው አንተን ለመያዝ የሚፈልግቱን ሞኞችና የዋሆች አንተው እራስህ ሞኝ ሆነህ ሞኝ መስለህ ቀርበኻቸው ቀስ ብለህ አረሳስተህ ማጅራታቸውን ለቀም አድርገህ ተቆጣጠራቸው።


ሁል ጊዜ ወዳጅ መስለህ ሰውን ሁሉ አስተናግድ ። ግን እነደ ሰላይ ጆሮህን ሰጥተህ የሚናገረውን በደንብ አዳምጣው።


ጠላትህንና ተቀናቃኝህን እጅህ አስገብተህ አለአንዳች ርህራሄ እሱን ደምስሰው። ፍጀው።

ሰዎች በአንድ ነገር እንዲያምኑ ሁልጊዜ ፈትፍተህ ቀባብተህ አንዳች ነገር አቅርብላቸው። በዚያውም ልባቸውን በልተህ እምነታቸውን በአንተ ላይ ገንብተው እንዲከተሉህ አድርጋቸው።

ሌሎቹን ደግሞ አንተው ፐውዘህ ደበላልቀህ የምትሰጣቸውን ካርታ ብቻ ይዘው –ከቁጥጥርህ ሳይወጡ እንዲጫወቱ እነሱን አድርጋቸው።

ሰዎች የተደበቀ ሕልምና ምኞት አላቸው። ይህን አውቀህ ገና ለገና ይመጣል ብለው የሚመኙትና የሚቋምጡትን ሐሳቦች ሁሌ እያነሳህ አጓጓቸው።“

በመጨረሻም- አርባ ስምነቱን የሮበርት ግሪንን ዝርዝር „ተንኮሎችን“ እናሳጥረው- „ …እረኛውን ጠብቀህ ሳያስበው አናቱን ብለህ ቀጥቅጠህ ግደለው። ያኔ በጎቹ ደንግጠው በያለበት ፈርጥጠውና ተበትነው ሁዋላ የሚገቡበት አጥተው በደጅህ ያድራሉ።“ sheepብሎ የሦስት ሺህ ዓመቱን ብልሃት በዚህ ዓረፍተ ነገር ይዘጋል።

አስተዋይ አንባቢ እንደሚረዳው እንደዚህ ዓይነቱ የአምባገነኖች ተንኮል በአውሮፓና በአሜሪካ አሁን በያዝነው በ21ኛው ክፍለ ዘመን -ተዘዋውረን ስንመለከተው አንድም ቦታ -ቢያንስ በአገራቸው- ተከታይ የለውም።

በአፍሪካ ግን እንደምናውቀውና ተጨባጩ ሁኔታ እንደሚያሳየው ለአንድ አምባገነን ለዚያም አስተሳሰብ ልቡን ለሸጠ ሰው ይህ ብልሃት አሁንም ቢሆን እነደ አለፉት ሺህ አመታት ትልቅ ቦታ አለው።

በአሜሪካና በአውሮፓ አንድ አምባገነን መሪ እላይ የተጠቀሱትን መመሪዎች መሠረት አድርጎ ሥልጣን ላይ ለመውጣት ወይም ሥልጣን ላይ ለመቆየት ይህን ያህል መድከም አያስፈልገውም አልን እንጂ አንድ የፋብሪካ ሥራ አስከያጅ በጀርመን ሆነ በፈረንሣይ ወይም የሠራተኛ ማህበር ተጠሪ በስፔን ወይም ለተወሰነ አመት የተመረጠ የድርጅት መሪ ወይም አንድ የሃይማኖት አባት፣ የጦር አዛዥ…አስተማሪ ወይም ሐኪም…አጠገቡ ያሉትን (ከቦታ ቦታ ይለያያል) ተንኮሉን እያውጠነጠነ አንዱን አቅርቦ ሌላውን አርቆ እነሱን እርስ በራሳቸው ሥልጣኑን መከታ አድርጎ ተብትቦ መከራ ፍዳቸውን አንድ በአንድ ተራ በተራ ሊያሳያቸው ይችላል።

እሱ እራሱ ደግሞ በተራው በሌላው ከበላዩ በአለው አንዳች ኃይል መዳፍ ውስጥ ወድቆ ጥዋት ማታም ተሰቃይቶ ሊያለቅስም ይችላል።

ግን እዚህ ሕግ በሚከበርበት አገር ሕግም ያለበትና ያ ሕግ በትክክል መተርጎሙ በሚመረመርበት ቦታዎችና አካባቢ አንድ ሰው ዕድሜ ልኩን እያለቀሰ እያማረረ ሕይወቱን አይገፋም። ጠበቃ ይዞ መከራከር ይችላል።…ይከራከራል። ታሪኩን ለነጻ-ጋዜጠኞች አቅርቦ ተራው ሕዝብ እንዲፋረደው ያደርጋል። ካሣም እስከ መጠየቅ ሰውዬውንም እሰከ ማስቀጣት ይሄዳል።

ግን ለእኛ ጠቅላላውን ሁኔታ ለመገንዘብ „ሥልጣን ምንድነው?“ ብለን እንጀምራለን።

„ ሥልጣን ከየት ይመጣል? ሥልጣን የአንድን ሰው ባህሪና ተፈጥሮ እንዴት ይቀይራል ። ለምንስ ይቀይራል?

ለምንድነው አንዳንድ ሰዎች ሥልጣንን የሚወዱት? ለምንድነው እነሱ ከሥልጣንም አንወርድም ብለው ተኩስ የሚከፍቱት? ለምንድነው ሌሎች ሰዎች ሥልጣንን እንደ ጦር ፈርተው የሚሸሹት?…አምባገነኖች ከሥልጣን አንወርድም አንለቅም ብለው ሲሟገቱ፣ ለምንድነው ሌሎቹ ከሥልጣን በገዛ ፈቃዳቸው ለመውረድ ወይም ለማስረከብ ዝግጁ የሚሆኑት?“

„ሥልጣን እንደ ሞቀ ወሃ እንደ ወርቅ ሓብት ትጥማለች“ የሚባለው አነጋገር ዕውነት ነው ወይ?… የሥልጣን ሰዎች በሙሉ አታላይ ናቸው የሚባለውስ አነጋገር ምን ያህል ዕውነት ነው?

ሥልጣን እንደ „ሴሰኛ“ የሚያሳብድ “በሽታ” ነው ይባላል። ይህስ ዕውነት አለው ?“
እነዚህንና እነዚህን የመሰሉ ጥያቄዎች አንስተን „ስለ ሥልጣንና የሥልጣን ተሸካሚዎችን ሰዎች ባህሪና ተፈጥሮ“ እንመለከታለን። የሥልጣን ሰዎች ምንድንናቸው?
አነሱን ከእኔና ከአንተ ምን ይለያቸዋል?

„በእግዚአብሔር የተመረጠ“ መሪ አለ። ይህስ እውነት ነው? በጠበንጃ ዕድሉን ሞክሮ እዚያ ላይ የተሰቀለ ሰው አለ። ይህ ስለሆነ ዕድሜ ልኩን ሥልጣን ላይ መቀመጥ አለበት?

ለአንተ የሚሆንንህን ጥሩ ሠርዓት እኔ አውቅልኻለሁ የሚሉ ቡድኖች አሉ። ይህን ሲሉ ዕውነታቸውን- ከልባቸው ነው? ለመሆኑ ለእኔ የሚስማማ ምን ዓይነት ሥርዓት ያመጡልኛል?… ምኑን ነው? የትኛው ነው? ለእኔና ለአንተ የሚሆን ጥሩ ሥርዓት? የተለያዩ መፍትሔ ይዘው ከቀረቡት ድርጅትና ሰዎች መካከል የትኛው ነው ትክክለኛው? የቱን አንማንን? የቱን እንከተል?

ሊንዲ እንግላንድ የምትባለው ያቺ የኢረቅን እሥረኞች በአቡግሬብ እሥር ቤት lindy-iraqእንደ ውሻ ሰንሰለት አንገታቸው ላይ አሥራ በአራት እግራቸው ራቁታቸውን ሳታስኬዳቸው በፊት አንድ የአገሩዋ ሰው የአሜሪካው የሳንፎርድ ዪኒቨርሲቲ አስተማሪና ተመራማሪ „…እንደዚህ ዓይነት ጭካኔ ከየት ይመጣል ? ሥልጣንና ጭቆና የተሞላበት ፈላጭ ቆራጭነት መነሻ ምክንያቱ ምንድነው? ምን ይሆን ከጀርባው ያለው ነገር? „ ብሎ ለጥያቄው መልስ ለመስጠትና ለመመራመር አንድ መንገድ ተከትሎ ነበር። እሱ በጥቂት ቀናት ምርመራው የደረሰበት ውጤት ያስደነግጣል።

ፕሮፌሰር ፊልፕ ሲምባርዶ አውጥቶ አውርዶ በሚያስተምርበት ዩኒቨርስቲ ቀደም ሲል በ1971 ዓ.ም. (እአአ)ለምርመራው ፈቃደኛ የሆኑ ወጣቶችን እፈልጋለሁ ብሎ አንድ ማስታወቂያ ያወጣል።psychologie
ያን„ ከሃያ አመት በላይ የሚሆኑ ወንዶች የሳይኮሎጂ ትምህርት ተማሪዎችን እፈለጋለሁ“ የሚለውን ማስታወቂያ ተመልክተው ከሰባ በላይ የሚሆኑ ወጣት ጎረምሶች መልስ ይልኩለታል።

ምሁሩም ለእሱ ምርመራ የሚፈልገውን ጥሩ ክራይቴሪያ – አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን ያሟላሉ የሚላቸውን 24 ልጆች መርጦ ሌሎቹን አሰናብቶ (ምናልባት መድሓኒት በየጊዜው የሚወስዱትን አልፈለግም ብሎ ይሆናል) ወደ ሥራ ይራመዳል።

በ1971 እ.አ.አ ዓ.ም በወጣው ጥናቱ ላይ እንደተነበበው ሥራውን በሁለት ቡድኖች ከፍሎ ይጀምራል።

በመጀመሪያ ተማሪዎቹን ዝም ብሎ ለሁለት ቡድን እጁ እንደአመጣለት ሰንጥቆ ከፊሉን ቡድን አሥራ ሁለቱን በአንድ በኩል ሌላውን አሥራ ሁለቱን በሌላ ወገን አቁሞ ሳንቲም ወደ ላይ በመወርወር „ዘውድ“ ያሉትን „የወህኒ ቤት“ ዘበኛ -ፖሊስ ያደርጋቸዋል።

„ጎፈር“ ያሉትን ደግሞ„እሥረኛ“ አድረጎ የተመደበላቸውን „ጨዋታ“ እንዲጫወቱ ሜዳውን አዘጋጅቶ ወደ ዩኒቨርስቲው ምድር ቤት ወደ እሥር ቤቱ እነሱን አሰናብቶ ለሚቀጥሉት 14 ቀናት ፖሊሶቹን በተለይ „በእስር ቤቱ ውስጥ ጸጥታ እንዳይደፈርስ ረብሻ እንዳይነሳ የጠበቀ ቁጥጥር እንዲያደርጉ „ ትዕዛዝ ሰጥቶ ሁለቱንም ቡድን ይልካቸዋል።

ሁሉም ነገር ዋዛና ፈዛዛ የልጆች ጨዋታ እንዳይሆንና ዝብርቅርቁ ወጥቶ ድካሙ ከንቱ እንዳይሆን „…የእሥረኞቹን ቡድን“ የፖሊስ ዩኒፎርም በለበሱ ሰዎች አስይዞ ጸጉራቸውን አስላጭቶ ልብሳቸውን እሰከ የውስጥ ሱሪ ድረስ አስወልቆ ስስ የእሥረኛ ቀሚስ አልብሶ የራሳቸውን ቅል በስቶኪንግ ሹራብ ሸፍኖ በብረት በተሰራው ቀፎ ውስጥ ማንም እሥረኛ መብቱን ተገፎ እንደሚወረወረው እነሱን እዚያ የዩኒቨርስቲ ምድር ቤቱ ውስጥ ይወረውራቸዋል።

ለፖሊሶቹም ዱላና ጥቁር መነጽር ዩኒፎርምም አልብሶ እሥረኞቹን እንደ ገና „በደንብ እንዲቆጣጠሩ „ትዕዛዝ ስጥቶ እሱ ተደብቆ የሚያይበት የምርመራ ጠረጴዛው ክፍል ይመለሳል።

የመጀመሪያው ቀን -እሱ እነደ ጻፈው- በሰላምና በቀልድ በሳቅና በጨወታ ወሬአቸውን -ፖሊሶቹም እሥረኞቹም – እየከኩ ሌሊቱን ያሳልፉታል። የሚቀጥሉት ቀናት ሌላ መልክ ይይዛል።

በሁለተኛው ቀን የእሥረኛ ጠባቂ ፖሊሶቹ ሥራ ከምንፈታ፣… ዝምታውስ ለምንድነው ? ብለው አንዳንድ የተንኮል ሓሳብ – በአንዳንዶቹ አእምሮ ብቅ ይላል። ይመጣል።
ከምሽቱ ስምንት ሰዓት ማለት ከእኩለ ሌሊት በሁዋላ እሥረኞቹን ዓለም ጤና ብለው ከተኙበት ጥሩ እንቅልፋቸው ለመቀስቀስ ፖሊሶቹ ይስማማሉ። የብርድ ልብሳቸውን ገፈው ቀስቅሰው „ተነሱ! …አልጋችሁን በትክክል እንጥፉ!“ እያሉ እየተቆጡ አልነሳም ያሉትን እሥረኞቻቸውን እያዋከቡና እየገፈተሩ ያላገጠውንም መርጠው አውጥተው እንደገና ደግሞ ደጋግሞ አንሶላውን እንዲያስተካክል እያስገደዱ ሌሊቱን እነሱ ዘበኞቹ እየሳቁ እንቅልፍ ነስተዋቸው ያድራሉ።
ይህን የጠነሰሱት ፖሊሶቹ ከሌሊት ሥራቸው ተመልሰው አልጋቸው ላይ ቀኑን በሙሉ ተኝተው ያሳልፋሉ።

በዚህ የተሰበሳጩትና ለመተኛት ያልቻሉት እሥረኞች በተነጋተው አድማ መተው ከአልጋቸው አንነሳም፣ ክፍላችውንም አንጠርግም ደረታቸው ላይ የተለጠፈውን (ስም ሳይሆን በቁጥር ነው የሚጠሩት) የእሥረኛ መለያ ቁጥራቸውን ቦጭቀው ወርውረው… የቀን ተረኞቹን ዘበኞች የፖሊሶቹን ትዕዛዝ አንቀበልም ፣አንሰማም ብለው በአመጽ ያስቸግራሉ።

ይህን በማድረጋቸውም የፖሊሶቹ አዛዥ የአድማው መሪ/መሪዎች እነማን እነደሆኑ ፈልጎ አውጥቶ ለመቅጣት ምርመራ ይጠራል።

ቀስቃሽ አድመኞቹን በአንዴ ነጥለው አውጥተው ፖሊሶቹ ብርሃን የማያገኙበት ጨለማ የቁም ሳጥን ውስጥ ወርውረው ያስገቡዋቸዋል ።

በሦስተኛውና በአራተኛው ቀን አንዳንድ እሥረኞች የዘበኞቹን የቀንና የሌሊት የእንቅልፍ መንሳት ተንኮል ቁጣና ቅጣት የሚደርስባቸውን በደል መቋቋም አቅቶአቸው „እሥር ቤቱን ለቀን እንውጣ“ ብለው መጮህ ይጀምራሉ።
ይባስ ብለው ጸጥታ አስከባሪዎቹ ፖሊስ ይህን የእሥር ቤት ጸጥታ በኃይል በዱላና በተለያዩ ቅጣቶች ለማስከበርና ለመቆጣጠር ሌላ ያልታሰበ የእሥረኞቹን ቅስምና ሞራል የሚሰብር ከፍተኛ እርምጃ ተመካክረው ይዘው ይቀርባሉ።
ክፍሉን በእሳት ማጥፊያ ጢስ ያፍናሉ። ወሃ ይረጩአቸዋል። psychopath

ሞቃት አየር ወይም ብርድ ይለቁባቸዋል።
ይህን ሁሉ ነገር የእሥረኞቹ ጩኸት ተመራማሪው በቪዲዮና በድምጽ መቅጃው ቴፑ እሱ በተከለው ካሜራ በቀደደው ቀዳዳ በፊልሞቹ ቁጭ ብሎ ፖሊሶቹና እሥረኞቹ የሚሰሩትን ሥራ ሁሉ አንድ በአንድ እየመዘገበ ይከታተላል።

አንደኛው እራሱን ስቶ አስተማሪውን ላነጋግር ብሎ ለምኖ ከተመራማሪው ጋር ተገናኝቶ እሱን እንዲያሰናብተው እግሩ ላይ ወድቆ ይለምነዋል።
ተመራማሪ አስተማሪውም „…አይዞህ ትንሽ ቀናት ነው፣ ቻለውና ቆይ። አንተን የእኔ ሰላይ ነው ብዬ …እነግራቸዋለሁ።ምንም አትሆንም በርታ…እኔ አለሁልህ!“ ብሎ አታሎት ወደ ምድር ቤቱ ወደ ገራፊዎቹ በገዛ ፈቃዱ እንዲወርድ መልሶ ይሸኘዋል።
እየመሸ ሲነጋ ቀኑም እየገፋ ሲሄድ እሱና አንዳንድ ልጆች በየጊዜው እየተቀያየሩ ፍዳቸውን የሚያሳዩትን ፖሊሶች ጭቃኔ መቋቋም የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ።

ፖሊሶቹም በጀመሩበት የጭቃኔ ሥራ ቀጥለውበት -ጥናቱ እንደሚለው- በየቀኑ አዳዲስ እያውጠነጠኑና እየጨመሩበት የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸውን ሕይወት ሲኦል ውስጥ እንደተወረወረች ነፍስ አለአንዳች ርህራሄ ወደማሰቃየቱ ይሸጋገራሉ።
አንዱማ ፖሊስ ልብሳቸውን አውልቀው ራቁታቸውን እንዲተኙ ያዛል። ሌላው የሽንት ቤቱን መቀመጫ ሳህን በእጃቸውና በእስረኛ ቀሚሳቸው እንዲጠርጉት ያዛል። ሌላው ከመሬት ተነስቶ እላያቸው ላይ ተቀምጦ ሃያና ሰላሳ „ፑሺ አፕ ጂምናስቲክ“ ከአልጋቸው ወርደው እንዲሰሩ ያዛቸዋል። ዕንቅልፍ ከመንሳት አልፎ ሌላም ቅጣት በየቀኑ እያሰቡ ይቀጡአቸዋል።

በሚቀጥሉት ቀናት እሥር ቤቱ በክቶ በሽንት ባልዲና በሠገራቸው እንዲከረፋ አድረገውታል። አንዳንዶቹ እሥረኞችን እራሳቸውን ስተው አብደው ብቻቸውን -ይኸው ጥናት እንደሚለው- ማውራት ጀምረዋል።

በመካከሉ አንዱ ፖሊስ ማንም ሥራዬን አያይም ብሎ -በፊልም ግን እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ይቀረጻል- እሥረኞቹን (ጓደኞቹን) ጥናቱ ላይ እንደተጻፈው „አብረው ተኝተው የግብረ ሰዶም ሥራ እየተፈራረቁ እንዲሰሩ ያስገድዳቸዋል።”

ኤክስፐርመንቱ የሰው ልጅ ሥልጣንና ኃይል በአንዱ ላይ ከአለው እሰከ ምን ድረስ ይሄዳል? የሚለው ምርመራ አንዲት የዩኒቨርሲቲው አስተማሪ ሴትዮ እሱዋ በአነሳቸው ጥያቄ – ልኩን እያጣ ስለሄደ- ሌላ ደረጃ ላይ ሳይደርስ እንዲቋረጥ ይደረጋል።
እሱዋም „…በምን ዓይነት የሒሊና ጭንቅላትህ ነው? አንተ ይህን ሁሉ ነገር የምታደርገው?… ሞራልህ ለመሆኑ አይወቅስህም ወይ? …እንዴት በተማሪዎች ሕይወት ትቀልዳለህ?“ ብላ ባቀረበችለት ጥያቄ ፣አስተማሪው ደንግጦ ምርመራው እንዲቋረጥ ተደርጎአል።
ለካስ ሳያውቀው እሱ እራሱ ተመራማሪው አስተማሪ ፕሮፌሰር ሲምባርዶ ነገሩ ጥሞት „…ተባባሪ ፣ …ጨካኝ የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪና አዛዥ የእሱን ቦታና ሥልጣን…“(አብዛኛው እንደዚህ ነው) ሰተት ብሎ ገብቶ ይዞ ተቀምጦ ልጆቹ ሲሰቃዩ እሱ ምንም ሳይሰማው ያይ ነበር።
አንዱ „ፖሊስ“ ሁኖ በምርመራው ላይ የተሳተፈው ተማሪ እንዴት ቀስ እያለ እሱ ሳያውቀው ወደ ጨካኝ ግን ደስ እያለው እሱ ወደ „ሳዲስድትነት“ እንደተቀየረ በማስታወሻ ደብተሩ ላይ አስፍሮ ነገሩን እንደዚህ አደድርጎት አስቀምጦታል።
„…እኔ በተፈጥሮዬ ሰላም ወዳድ ማንም ሰው ለመጉዳት የማልፈልግ ፍጡር በመሆኔ እሥረኞቹን አለአግባብ ለማሰቃየት ምንም ዓይነት ፍላጎት የለኝም ። በደልንና ጭካኔን ፓሲፍሲት ስለሆንኩ የማንንም ጦርነት እኔ አልደግፍም።ሰው ለምን ጨካኝ እንደሚሆን አይገባኝም…“ የሚለውን አቋሙን ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ደብተሩ ላይ ይህ ወጣት አሥፍሮ ነበር።
ከሦስት ቀን በሁዋላ ደግሞ„…ለመጀመሪያ ጊዜ በሕይወቴ ሥልጣንን መከታ አድርጌ ደስ ያለኝን ነገር እንደ ልቤ ለማድረግና ለማዘዝ ትዕዛዜም በሥራ ላይ እንዲውል ያገኘሁት የበላይነት ምን ያህል የሚያረካና ደስ የሚያሰኝ መሆኑን የተረዳሁት አሁን ነው።…ትዕዛዜን ተቀብለው እሥረኞቹ የተባሉትን ሁሉ ያደርጋሉ።አይገርምም…ደስ ሲል…“ የሚለውን አረፍተ ነገሩን ይኸው ልጅ የማስታወሻ ደብተሩ ላይ ያሰፍራል።

እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም በዚያች በአገኙት የትንሽ ቀናት የሥልጣን ሰዓታቸው ሕልማቸውንና ምኞታቸውን – ፋንታዚያቸውን በደንብ ለቀውት በሥራ ላይ- እላይ እንደ ተጠቀሰው ፖሊሶቹ ሊተረጉሙት ችለዋል። እንዲያውም ፉክክር ውስጥ ገብተው „እኔ እበልጣለሁ እኔ አውቅበታለሁ“ ውስጥ ደርሰዋል።
ለሁለት ሳምንት የታሰበው ኤክስፐርመንት በስድስት ቀናት ጊዜ ውስጥ የተቋረጠውም በዚሁ „በሥልጣን መባለግ“ ቁጥጥር የሌለው ጭካኔ በዪኒቨርሲቲው ምድር ቤት ውስጥ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በመምጣቱ ነው።
amnesty_international_candle በዕውነተኛው ሕይወት፣ በአፍሪካ -ለዚህ ነው ታሪኩን ያነሳነው- አምኒስቲ እንተርናሽናልና ሒውመን ራይት ወች በየአመቱ እንደሚሉት ከዚህ የባሳ ነው።

ሥልጣንን ምን እንደሆነ እና ሥልጣን ይዞ በሰው ልጆች ሕይወት ላይ አለርህራሄ የጭካኔ መዓት ማውረድ ምን ማለት እንደሆነ የሒትለርንና የዮሴፍ ስታሊንን ደርጊት እንደገና መለስ ብሎ ማስታወስ በቂ ነው።

የሩዋንዳው ፍጅት ሌላው የ20ኛው ክፍለ ዘመን ከላይኞቹ ጋር እንዳይደገም ጥሎልን የሄደው አሳዛኝ ትምህርት ነው።
በመደብ ትግልና በዘር ጥያቄ አሁን ደግሞ በሃይማኖት ሳቢያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንዴት እንደጠፋ- ገና በቂ ምርምር አልተደረገበትም- እንዴት እንደነበር መገመት ቀላል ነው።

ምንድነው እላይ ከቀረቡት ተማሪዎች ልብና እታች ከተጠቀሱት የመደብና የዘር ልዩነት ቲዎሪ አራማጆች መካከል ያለው „ልዩነትና አንድነት“?

በሁለቱም በሦስቱም መካከል ያለው „አንድነት“ አንድ አመቺ ሁኔታ ቁጥጥር የማይደረግበት ቦታና ሥፍራ… እራሱ ሕግ አውጪ እራሱ ሕግ አስፈጻሚ እራሱን በእራሱ ከሕግ በላይ ያደረገ ሰው የፈለገውን ከማድረግ እንደማይመለስ የሚያሳይ ነው።
ይህም ማለት አመች ሁኔታ አንድን ሰው እዚህ እንደሚባለው „ሌባ“ እንደሚያደርገው ሁሉ፣ አመች ሁኔታ:- የሚቆጣና የሚቆጣጠር ሕግና ሥርዓት በሌለበት ቦታና አካባቢ በዚያች አገር አንድ ሰው ሥልጣኑን በእጁ እስከ እሰከ አስገባ ድረስ የፈለገውን ከማድረግ የሚመልሰው ምንም ነገር የለም።
በቅርቡ እዚህ ጀርመን አገር በፕሮፌሰር ቶማስ ኤበርት የኮንስታንት ዩኒቨርስቲ የኖይሮ-ሳይኮሎጂ አስተማሪ „የኮንጎና የሌሎች አፍሪካ አገር ነጻ-አውጪ ተዋጊዎች ታሪክን“ ተከታትሎ ተመራምሮ ያወጣው ጥናት ይህንኑ እላይ የተተረከውን „የተማሪዎች ታሪክ“ በሌላ መልኩ አቅርቦአል።
ሰውዬው ተዋጊ ወጣት ጦረኞቹን አነጋግሮና ጠይቆ ወደ ምርመራ ጣቢያውም ተመልሶ የብዙ ወንጀለኞችን አንጎል መርምሮ እንደደረሰበት ሰውን ማሰቃየት ሆነ አንድን ሰው ለመግደል (-ብዙ ምክንያቶች ከጀርባው አለ… ቅናት አለ እራስን ከጠላት መከላከል አለ… አለጥርጥር በአይዲኦሎጂ መሳከርም አለበት…) „አውሬን አድኖ ከመግደል ደስታ ጋር እንደተያያዘ“ ምሁሩ ይገልጻል።
ይህቺን „ደስታ“ ለማግኘት አንድ ጂን MAOA-GEN. ተጠያቂ እንደሆነም ይኸው ጠበብት ያነሳል። ይህ ጂን ግን ተጠያቂ ቢሆንም ፈንድቶ እንዳበጠብጥ እሱን የሚያግድ ሜካኒዝም አለ።Monoamine_oxidase_A_2BXS

ማንም ሰው ዕድሉን ከአገኘ „ገዳይ“ ለመሆን እንደሚችል ጥናቱ ይጠቁማል። … ለምድነው አንድ ሰው „ጨካኝ“ የሚሆነው? ሌላውስ ለምንድነው ፍዳ ተቀባይ የሚሆነው?

ይህ እንዳይሆን ይህን ለማገድና ለመቆጣጠር ምን ዓይነትና ብልሃትና ሕግ በእጃችን አለ?

በእጃችን የሚገኘው የጽላተ- ሙሴ ሕግጋት አንደኛው ነው። „…አትስረቅ አትግደል አትመኝ…“የሚለው የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስትያን የያዘቺው ታቦት እንደ ምስክርነት ሊጠቀስ ይገባል።
ይህ በታሪካችን የመጀመሪያው አመታት ላይ ብቅ ብሎ „አብሮ የመኖርን ሥርዓትና ደንብ“ መልክ ሊሰጠውም ችሎአል ። እሱ -ሕግጋቱ ብቻውን ግን “በቂ መተዳደሪያ አይደለም።”

የአዶልፍ ሒትለር ፖለቲካና የናሺናል ሶሻሊዝም ፍልስፋና የናዚዎቹ ርዕዮተ-ዓለም ወረድ ብለን እንደምንመለከተው ይህንኑ „…አትግደል“ የሚለውን ሕግ እንደአለ -„ይህ የአይሁዶች ፍልስፍና ነው“ ብሎ አዶልፍ ሒትለር „ሰርዝቶት „ ፍጅት በእነሱ በአይሁዶችና በሌሎች ሕዝቦች ላይ ሊከፍት ችሎአል።

አተይስት- ኮሚኒስቶቹም እነ ስታሊንና እነ ማኦ እነ…ከዚህ ያልተለ እርምጃም እነሱ በዘመናቸው ወስደዋል።“…አትግደልና ጠላትህን እንደራስህ አድርገህ ወደደው…“ ከሚለው ሕግ እራሳቸውን አርቀው እንደዚሁ በተራቸው እነሱም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት – በሩሲያ በቻይና በካምቦጂያ በኮሪያ በኢትዮጵያ በቬትናም አሁን በኮንጎ በናይጄሪያ በሱማሌ…ፈጅተዋል።
ሒትለርና ስታሊን ከመፈጠረቸው በፊት የጀርመኑ ስመ ጥሩ ጸሓፊ ቮልፍጋን ጉተ ስለ አንድ „ኃይለኛ አጋንንት“ ያ ሰውን ሁሉ አታሎ ስቦና ማርኮ እሱ ባሪያው አድርጎ ስለሚገዛቸው ፍጡር ፣…ጽፎአል።
ይህ ሰውም እሱ ማን እንደሆነ? ምን ማድረግ እንደሚችል?…ቆይቶም ሊያመጣ የሚችለውን መዓት ጠቅሶ እሱም እንዴት በአንድ ዓለም አቀፋዊ ኃይል ሊባረር እንደሚችል አንስቶ ከእሱ ጋር ጉተ በጽሁፉ እኛን አስተዋውቆአል።
የጀርመኑ ደራሲ ጉተ ናፖሊዮንን አይቶ ስለ “ዴሞን” ሲጽፍ E.T.A. ሆፍማን የተባለው ሌላው የአገሩ ደራሲ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን „ሥልጣን ስለጠማውና ሥልጣን ከመያዝ ስለማይመለሰው አንድ ሰው“ እሱም በድርሰቱ ላይ አንስቶ ቸክችኮአል።
ይህም ፈላስፋው ፍሬደሪክ ኔቼ “ …ስለ ሥልጣን ጥማት“ ከመጻፉ በፊት የተነደፈ ሓሳብ ነበር።
„…ሕይወት ተንቀሳቃሽ ሕይወት ሁሉ ከትግል ጋር የተያያዘ ነው። ሕይወትም የትግል ውጤት ነው።ድል ሁሌ የጎበዙ እንጂ የደካማው ፍጡር አይደለም። ሌላውን ድል በማድረግም ጠንካራው ፍጡር ሥልጣኑንም ኃይሉንም ሐብቱንም ንብረቱንም ያበዛል። በዚህ መንገድ…ይበዛለታል። ይበረክትለታል።“
ኔቼ „…አስፈላጊ ያልሆኑትን ፍጡሮች በማጥፋትና በመደምሰስ አዲሱን ልዩ ሰው እሱን መፍጠር ይቻላል…“ ያለውን የፍልስፍና ፋንታዚ ሒትለር ብቅ ብሎ የኦሽዊትዝን ወህኒ ቤቶች መስርቶ „መኖር አይገባቸውም“ የሚላቸውን የሰውን ልጆች… አይሁዶችን ሲንቲና ሮማዎችን ጥቁርና ክልሶችን ደካማና በሽተኞችን እያጋዘ በእሳት ምድጃ -አዲስ „…አሪየን“ የተባለው „የጀርመኖች የነጭ ዘር ብቻውን ዓለምን እንዲገዛ „ እነሱን አጋይቶአቸዋል።konzentrationlager3


ለዚህም ድርጊቱ „ እግዚአብሔር የፈለገው ቅዱስ ሥራ ነው“ የሚለውን መጠሪያ ስምና አላማ ሰጥቶት በቅስቀሳ የሰውን ልብና አእምሮ አስክሮ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ጭካኔውን አካሄዶአል።

ቢያንስ ከሦስት ሺህ የተለያዩ መጽሓፍት በላይ ስለ ተጻፈለት ሒትለር (አሁንም እየተጻፈለት ነው) ብዙ አዲስ ያልተሰሙ ነገሮችን ፈልጎ ጨምሮ ለአንባቢው ማቅረብ ቀላል ባይሆንም የሒትለር የፖለቲካ ቲዎሪ የተገነባው በ18ተኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በተስፋፋው በኢቮሊሽን ቲዎሪ በዚያ ትምህርት ላይ መሆኑን መጥቀሱ እዚህ ላይ አስፈላጊ ነው።
ምክንያቱም ! ይህን የመሰለ „ዕብድ“ የተማሩና ያልተማሩ „ሰዎች“ እንዴት ታውረው እሱን በቀላሉ ተታለው ተከተሉት? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ በመሆኑ ነው።
„ተፈጥሮ ርህራሄ የማታውቅ ጨካኝና መራራ ፍርድዋን ቁርጥ አድርጋ የምትሰጥ“- ትግሌ- በሚለው የዘረኛ ፖለቲካ ድርሰቱ ላይ ሒትለር እንደጻፈው „ …ኃይለኛ ፍጡር ናት።…የቻለውና ጠንካራው – ጥረቱ ለመኖር ነውና- አሽንፎ ወጥቶ እራሱንና ልጆቹን ከጥፋት ያድናል። ደካማው ደግሞ ወድቆ ቦታውን ጊዜው ለወለዳቸው ጠንካራ ዘሮች ይለቃል።…ሰበአዊ ርህራሄ የሚባል ነገር በተፈጥሮ ትግል ውስጥ የለም።…ይህን የሚሉት ፈሪዎቹ ደካማዎቹ አጉል እናውቃለን ባይ ጥረዝ ነጠቆች ናቸው። የሰው ልጅ በማያቋርጠው ዘላለማዊ ትግል ውስጥ ገብቶ እዚህ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሶአል። ዘለዓለማዊ ሰላም በሚባለው ነገር መታለል የለበትም። በዚህ ሓሳብ ከተታለለ ደግሞ ነገ ተንኮታኩቶ ይወድቃል።“ …ይህ ግን መሆን የለበትም ብሎ በዚህ ዘለዓለማዊ ትግል አሪየር የተባለው የጀርመኖች ነጭ ዘር ከሌላው ደካማ ደምና ቀለም ጋር ሳይካለስና ሳይበረዝ ሳይነካካ አሽናፊ ሁኖ ወጥቶ ሌሎችን ደምስሶ -ኢቮሉሽን ላይ እንደምናየው- ዓለምን -ሒትለር መግዛት አለበት“ ይላል።
በዚህም ጠቅላላውን የአይሁድና የክርስቲያን ሃይማኖት፣ የግሪክንና የሮምን ሥልጣኔ እነሱ የመጡትን ኤቲክና ሞራል ፍልስፍንና አስተሳሰብ ሽሮ ሰርዞ አዲስ „የዘር“ ቲዎሪ ይገነባል።
ከዚያ በሁዋላ „ለመኖር ለመግዛት ለመስፋፋት …ያገኘኸውን ፍጀው „ ወደ የሚለው ፍልስፍናው ሒትለር ይሸጋገራል። የሩሲያ መሬት ለመስፈር ይገባናል ይላል።
አሥርቱ ቃላት ላይ የሰፈረው „አትግደል“ የሚለው ሕግና ደንብ „…እኛ ዓለምን እንዳንገዛ አውቆ በአይሁዶች የተላከብን አፍዝ አደንግዝ ትዕዛዝ ነው።… እሰከ ዛሬ ድረስ ያገለገሉት የሞራል ደንቦች ቦታ የላቸውም።የሲና ተራራ ላይ ሙሴ ከእግዚአብሔር ተቀበልኩት ያለው ጽላት በአሁኑ ዘመን ቦታ የለውም…“ ሒትለር ሲል ሒምለር የተባለው ጋሻ ጃግሬው የታጠቁትን የኤስ ኤስ የዘር የጽዳት ዘመቻ ጠራጊዎችን „ሂዱና ግደሉ“ ከማለቱ በፊት እንደዚህ ብሎ ሸኝቶአቸል።konzentrationlager2
„…ከፊታችሁ ወድቀው ተሰብስበው ከተከመሩት ከመቶ አስከሬን ፊት ብዙዎቻችሁ ስትቆሙ የሚሰማችሁን መገመት እችላለሁ። ወይም አምስት መቶው ተትረፍርፎ እዚያው ወድቆ ስታያዩት። ወይም ደግሞ አንድ ሺህ የሚጠጋው እዚያ እፊታችሁ ተጋድመው ስትቃኙአቸው። ነቅነቅ ሳትሉ ይህን እያያችሁ ኮርታችሁ ስትቆሙ -ይህ በማንም ታሪክ ላይ ያልተጻፈውን ጀግንነት ማንም ሰው በቃላት ገልጾ ሊያስቀምጠው የማይችለው ታሪካችሁና ታሪካችን ነው። በሉ ሂዱ …“ ብሎ ያሳናብታቸዋል።
ከዚሁ ጋር የውሽት ፕሮፓጋንዳው አብሮ ይለቀቃል።hitler2 ጠበንጃውና ቦንቡ ታንክና አይሮፕላኑ ይከተላል። ሁለተኛ ዓለም ጦርነት ይከፈታል። በዚሁ በተከፈተው ጦርነት ሳቢያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶአል።

ጥያቄው ትልቁ ጥያቄ ያ! ሒትለር የሚባል አንድ የሥዕል ትምህርት ቤት ለመግባት ዕድል ያላገኘ ሰው፣ ያ በሁዋላ ተራ ወታደር ሁኖ የአንደኛ ዓለም ጦርነት ውስጥ የተሳተፈ የፈላስፋዎችና የደራሲዎች አገር በሚባለው በጀርመን እንዴት በቀላሉ ሁሉንም ቡድኖች አሸንፎ ተከታዮቹን ሰብስቦ ሥልጣን ላይ እንዴት እሱና ፓርቲው ሊወጣ/ሊወጡ ቻሉ?
ለዚህ ጥያቄ ደግሞ መልስ ለመስጠት ሌላ ጊዜ የሚጠይቅ አርዕስት ነው።
ያም ሆኖ አንደኛውን መልስ ብቻ ለመጥቀስ„… የፖለቲካ መደቡ በዚያን ዘመን አለመስማማት „ ለእሱ ለሒትለር ምን ጊዜም የማይገኝ ዕድልና በር ከፍቶለታል።
ኮሚኒስቶቹ በዚያን ዘመን -በየዓይነቱ ነበሩ- እርስ በእራሳቸው ያኔ ይጣሉ ነበር።እነሱ አንድ ላይ ሁነው ሶሻል ዲሞክራቶችን፣ ሶሻል ዲሞክራቶች-እነሱም ለጉድ ብዙ የተለያዩ ነበሩ- እርስ በራሳቸው… ሊበራሎቹ ከአናርኪስቶቹ ሞናርኪስቱ ከኮንሰርቫቲቡ እነሱ ደግሞ በተራቸው ከንጉሡ፣ ንጉሡ ከሩሲያና ከእንግሊዝ ጋር…ሁሉም ተሰብስበው አንዱ ላይ እንደገና እነሱ እርስ በራሳቸው…በዚህ ትርምስ (ኢትዮጵያን ይመስላል) ሒትለር መጥቶ ሁሉንም ጭጭ አድርጎ ቤተ-መንግሥቱ ሊገባ ችሎአል።
መፍትሔውን ያገኙት መራራውን የናሺናል ሶሻሊዝምን የፋሽሽት የግፍ አገዛዝ ከቀመሱና የብዙ ሰው ሕይወት ከጠፋ በሁዋላ ነው።
ፓርላማ እና የፖለቲካ ነጻነት ሰበአዊ መብትና ነጻ-ጋዜጣ መቻቻልና መከባበር ጣምራ መንግሥት ማበጀትና ሕግን ማክበር…ይህ ሁሉ የመጣው ከ1945 ዓ .ም በሁዋላ ነው።
„ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጋችሁ ጥላችሁ ለእንደዚህ ዓይነቱ ሥርዓት ብቻ ተነስታችሁ ታገሉ…“ያሉ የጀርመን ጭንቅላቶች ቀደም ሲል በብዛት ተነስተዋል።
ስለእነሱም ወደፊት እናነሳለን።
ለአፍሪካም ያላትና የቀራት ምርጫ ይኸው የነጻ- ሕብረተሰብ መንገድ ነው።
freedom


ይልማ ኃይለ ሚካኤል

—-

ለ አእምሮ ሰኔ 2006 / June 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር 10

መልስ ካሎት/ Reply (to comments):

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s